sbid

የክልሉ መንግስት ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የማምረቻ እና የመሸጫ ቦታዎችን እንዲሁም የፋይናንስ አቅርቦት በማዘጋጀት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው፦ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

“ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ኢትዮጵያ ታምርት ” በሚል መሪ ቃል በሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የተዘጋጀ የ 2018 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ታምርት የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በንቅናቄ መድረኩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ሀገራችን ኢትዮጵያ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር በምታደርገው ኢኮኖሚ ያዊ ሽግግር አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ።

ኢንዱስትሪን ማሳደግ የሀገርን ኢኮኖሚና ሉዓላዊነት የሚያረጋግጥ ዋነኛ መሳሪያ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል። በተለይም በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሀገራችንን በአለማቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።

ባለፉት ዓመታት በክልሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለመፍጠር “የኢትዮጵያ ታምርት፤ እኛም እንሸምት” ንቅናቄ በመጀመር በክልሉ ያሉ እምቅ አቅም እና ምቹ ሁኔታዎች በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ሀገር ኢንቨስተሮችን እየሳቡ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የክልሉ መንግስት በዘርፉ የማምረቻ እና የመሸጫ ቦታዎችን እንዲሁም የፋይናንስ አቅርቦት በማዘጋጀት በቁርጠኝነት እየሰራ በመሆኑ፤ በክልሉ ያለውን እምቅ የኢንዱስትሪ አቅም በመጠቀም ከዚህ በበለጠ ዘርፉን ማሳደግ ከዘርፉ ተዋንያን እና ከባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ጉዳይ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ በአፅንዖት ጠቅሰዋል።

የሲዳማ ክልል የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ አሻግሬ ጀምበሬ እንዳሉት ሀገራችን ለረዥም ዓመታት ኢኮኖሚዋ በግብርና ላይ ብቻ የተመሠረተ ስለነበረ የሚፈለገው ዕድገት አልተመዘገበም ብለዋል። የለውጡ መንግሥት ለኢንዱስትሪው ዘርፍ በሰጠው ትኩረት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለዜጎች የስራ እድል የፈጠረ፤ የቴክኖሎጂ ሽግግር የተደረገበት፤ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ የተገኘበት በመሆኑ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ በክልሉ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ የተከናወኑ አበይት ተግባራትን የሚያመላክት ዶክመንተሪ ፊልም ለእይታ የቀረበ ሲሆን የመወያያ ሰነድም እየቀረበ ይገኛል።

ከዚህ ባሻገር ለቀጣይ 5 ቀናት የማቆይ “ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ከ160 በላይ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የተሳተፉበት ኤግዚቢሽን እና ባዛር በይፋ የሚከፈት ይሆናል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የፌዴራል፤ የክልል እና የዞን ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፤ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

Scroll to Top