የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን 13ኛ ዙር የስትሪንግ ኮሚቴ መድረክ በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ አካሂዷል።
በመድረኩ የ2017 በጀት ዓመት በጥሬ የግብርና ግብዓት አቅርቦትና ትሰስር፣ በኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን፣ በክህሎት ልማት እንዲሁም በምግብ ደህንነት ቁጥጥር በኩል በተቋቋሙ ግብረኃይሎች በኩል የተከናወኑ ተግባራትን በጥልቀት ገምግሟል።
በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊና የኮርፖሬሽኑ ስትሪንግ ኮሚቴ አባል አቶ ጎሳዬ ጎዳና በፓርኩ ለተመዘገበው አበረታች ውጤት ፓርኩ ከተገነባ አንስቶ የታለመለትን ዓላማ ለማሳካት በስትሪንግ ኮሚቴውና ግብረሃይሉ ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓል፤ እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል።
ከግብዓት አቅርቦት፣ ከገበያ ትስስር፣ ከቴክኖሎጂ ሽግግር እና የሰለጠነ የሰው ሀይል ከመፍጠር አንፃር የስትሪንግ ኮሚቴው አስተዋፅኦ ውሳኝ እንደሆነ አስረድተዋል።
የሲዳማ ኢንድስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኃይሉ የተራ በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ዓበይት ተግባራትን በተመለከተ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፤ የፓርኩን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ጥራቱን የጠበቀ የግብርና ግብዓት ከማቅረብና ወሳኝ ከሆኑ መሰረተ ልማቶች አቅርቦት አንፃር የነበሩ ማነቆዎችን ከመንግስትና አጋር የልማት ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመፍታት የተኬደበት ርቀት ተስፋ ሰጪ እንደነበር አንስተዋል።
የተጀመሩ አበረታች ተግባራትን ከግብ ለማድረስ ኮርፖሬሽኑ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግ ተናግረው፤ ወደ ፓርኩ የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን ለማቀነባበር ፍላጎት ያላቸው ባለሃብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን አብራርተዋል።
የስትሪንግ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ፓርኩ የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት አንስቶ ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠርና መሰል ግቦችን ከማሳካት አንጻር ያስመዘገበው ውጤት በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑን ጠቁመው፤ የባለሃብቱንና የአርሶአደሩን የጋራ ተጠቃሚነትን በማሳደግ ለላቀ ውጤት በቅንጅት እንደሚሰሩ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
መስከረም 13/2018 ዓ.ም የሲዳማ ክልል ኢንዱሰትሪ ልማት ቢሮ