የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎበኙ
የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል፣ የሚኒስቴር መስሪያቤቱ ሚኒስትር ዴታ አቶ ሀሰን መሀመድና አቶ ታረቀኝ በሉልታን እና የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጎሳዬ ጎዳና ጨምሮ ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ጋር በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ያለውን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
የጉብኝቱ ዓላማ ወደስራ የገቡትን በማበረታታት፣ በሂደት ላይ ላሉት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግና የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በቅርበት ለይቶ በመፍታት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
ቡድኑ በፓርኩ ያሉ የተለያዩ ስራ የጀመሩና በመጀመር ሂደት ላይ ያሉ የግብርና ግብዓት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን፣ በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችንና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ተዟዙሮ የጎበኘ ሲሆን፤ ለባለሀብቶች የሚገጥማቸውን የትኛውንም ተግዳሮት ለመፍታት ሚኒስቴር መስሪያቤቱ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አቶ መላኩ አለበል ገልጸዋል።
ከፋብሪካ የሚወጡ ተረፈምርቶችን መልሶ በጥቅም ላይ ማዋልና ዘላቂ የምርት አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ በሚቻልባቸው ሂደቶች ላይ በጥልቀት መስራት የተሻለ ገቢ ለማግኘት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ በፓርኩ ያለው ስራ አበረታች ነውም ብለዋል።
የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሉ የተራ በፓርኩ ያለው የኢንቨስትመንት መነቃቃት ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ተናግረው፤ በሁሉም ዘርፍ ኢንዱስትሪ ሚኒስተርን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በመርሃግብሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ አካል የሆነው የችግኝ ተከላ በፓርኩ ቅጥር ግቢ ተካሂዷል።
ሐምሌ 5/2017 ዓ.ም
የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ